ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ባለቤትነትና ተሳታፊነትን የሚያረጋግጥ ተግባር እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ባለቤትነትና ተሳታፊነትን የሚያረጋግጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ከመጡ ከአፋህድ አባላት ጋር ለሶስት ቀናት ያደረገውን ምክክር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ በሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያካተተና አሳታፊነትን የሚያረጋግጥ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በአማራ ክልል የሰላም አማራጭን የተቀበሉ አካላት በሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ የሚሆኑበት ዕድል መመቻቸቱን ተናግረዋል።

የሰላም አማራጭን የተቀበሉ አካላትም አሉኝ የሚሏቸውን 17 አጀንዳዎች በመሰነድ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።

ባለፉት ሶስት ቀናት የተሳካ ምክክር መካሄዱን ጠቁመው፤ በቀጣይም ከሌሎች ወገኖች ጋር ተመሳሳይ ምክክር ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአካታችነትና አሳታፊነት መርህ ሁሉም አካል የምክክሩ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም