ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ነው
ሮቤ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግና ለዘርፉ ተግዳሮቶች በጥናት መፍትሄ ለመስጠት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ከአርሶ አደሮች የምርምር ኮንፈረንስ ጎን ለጎን የግብርና ምርቶች እና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለማስተዋወቅ ያዘጋጀው አውደ ርዕይ ተከፍቷል።
አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግን ግብ አድርጓ እየሰራ ነው።
ለዚህም የአርሶ አደሮችን ሀገር በቀል እውቀት በምርምር በማስደገፍ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአውደርዕዩ ጎን ለጎን አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የምርምር ኮንፈረንስ መካሄዱን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለድርሻዎች በአርሶ አደሩ ሀገር በቀል እውቀት ላይ ለምርምር የሚሆን መነሻ ግብአት እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ብለዋል።
የአርሶ አደሩን ችግር መሰረት ያላደረገ የምርምር ሥራ የተሟላ እንደማይሆን ገልጸው፣ አውደ ርዕዩና ኮንፈረንሱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተደገፈ ግብርናን ለማስፋፋት ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ-ብዙ ድጋፎችን በማድረግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው በአይነቱ ልዩ የሆነው የአርሶ አደሮች የምርምር ኮንፈረንስና የልምድ ልውውጥ መድረክ ለክልሉ ግብርና ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ በተከፈተው አውደ ርዕይ የአርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ምርቶች፣ በሰብል ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ በሽታዎች ፎቶ ግራፍና መከላከያ መድሀኒቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የግብርና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችም በአውደ ርዕዩ ላይ ለእይታ መቅረባቸው ታውቋል።