ቀጥታ፡

የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ሚና ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የአህጉሪቱን ትርክት በባለቤትነት ለመምራት የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን የፓናል ውይይት ተሳታፊዎች ገለጹ።

በፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa) ሚዲያ እና በኤ.ጂ.ኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ትብብር የተዘጋጀው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡና በድምሩ 321 ሚሊየን ተከታዮች ያሏቸው 61 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም 150 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ በጉባኤው ታድመዋል።


 

በጉባኤው ላይ "የአፍሪካን አዎንታዊ ገጽታ መገንባት" በሚል ርዕስ በተካሄደው የፓናል ውይይት፤ ታዋቂው ጋናዊ የይዘት ፈጣሪ በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር (ዎዴ ማያ) "ታሪካችንን እንዲነግሩልን ሌላ አካል መጠበቅ የለብንም" ሲል ተናግሯል።

ትኩረቱን ዘወትር በአዎንታዊ ታሪኮች ላይ በማድረግ የአፍሪካን ውበት ለዓለም እያስተዋወቀ እንደሚገኝ የገለጸው ዎዴ ማያ፣ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ለውጦችን በራሱ ተነሳሽነት በቪዲዮ መዘገቡንና ስራዎቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘታቸውን አስታውቋል።

የአፍሪካ መንግስታት ለሀገር በቀል ይዘት ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አሳስቧል።

የ2025 የዓለም ቆንጆ (Miss World Africa) ሀሴት ደረጀ በበኩሏ፤ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ መድረኮች የራሳቸውን ማንነትና እሴት ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው ገልጻለች።


 

ትክክለኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚቻለው የራስን ባህል፣ ቋንቋ እና እሴት ሳይሸራርፉ ለዓለም ማቅረብ ሲቻል መሆኑንም አስገንዝባለች።

ከቱሪዝም ሚኒስቴር የመጡት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በበኩላቸው፤ መንግስት የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችን ቁልፍ አጋር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህል መዳረሻ ብቻ ሳትሆን የወደፊት ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን ማሳየት እንደሚገባ ገልጸዋል፡

አፍሪካን በተመለከተ ሲነገሩ የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ወደ ዕድገትና ፈጠራ ትርክት መቀየር እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም