የአፍሪካን እውነት ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን እውነት ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካን እውነት ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
ጉባኤውም ኃላፊነት የሚሰማቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጠናከር፣ ትብብርን ለመፍጠርና የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግብን ለማሳካት ያለመ ነው።
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አፍሪካ የራሷን ትርክት በራሷ ለመገንባት፣የአህጉሪቱን እምነት የሚያሳድጉ ውጤቶችን ለማስመዝገብና የአፍሪካን መለያ ለመፍጠር የጋራ ምክክር ያደርጋሉ።
በጉባኤው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፣ የኤ.ጂ.ኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመዳ ኦላና፣ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
በጉባኤው ላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በማህበራዊ ሚዲያ የይዘት ዝግጅቶች ላይ ያለውን አስተዋጽኦ የሚዳስስ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የናቹራል ላንጉዌጅ ፕሮሰሲንግ ምርምር ዲቪዥን ዳይሬክተር ሳሙኤል ራህመቶ፤ ቀደም ሲል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለባለሙያዎች የቴክኒክና የምርምር ሥራ ይውል እንደነበር ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ የማህበረሰቡን የዕለት ተእለት የሥራ እንቅስቃሴ ቀለል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣን ዕድገትም ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የፕሮዳክሽን ሥራዎችን የሚያከናውን ምኅዳር በመፍጠር እንደ ሲኒማ የሚታዩ ምስሎችን መፍጠር እያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምስልና ድምፅ የማመንጨት አቅም ዕድገት የይዘት ፈጣሪዎችን ሥራ እያገዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለይዘት ዝግጅት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለአህጉሪቱ ትርክትና ገፅታ ግንባታ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአህጉሪቱን እውነተኛ ባህልና ታሪክ ለዓለም ማህበረሰብ ለመተረክም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ሌላኛው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ብራያን ጆታ በበኩሉ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጠራን በማላቅ የዲጂታል ክህሎትን የሚያበለፅግ የቴክኖሎጂ አማራጭ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም የአፍሪካን እውነተኛ ገፅታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዲጂታል አማራጭ ክህሎትን በማሳደግ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
ቦትስዋናዊው ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪ ዊሊያምላስት ኬ.አር.ኤም፤ የይዘት ፈጠራ ሥራዎችን ከገንዘብ ማግኛና ቁጥር ባሻገር ለአህጉሪቱ ትርክት ግንባታ መጠቀም አለብን ብሏል።
ለዚህም የሥራ ፍቅር ባህልን በማዳበር የዲጂታል አማራጮችን የአፍሪካን የተሻለ ገፅታና ትርክት በሚያጎላ መልኩ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጿል።