ቀጥታ፡

ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል የዘመኑ ብሔራዊ አርበኝነት ነው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል የዘመኑ ብሔራዊ አርበኝነት መሆኑን የአዲስ መሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል አገልግሎት ሠራተኞች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የመጀመሪያውን የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት ማስጀመራቸው ይታወቃል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

ማንኛውም ሰው በመሶብ የአንድ ማዕከል ሲገለገል ለኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ዕድገት ምስክርነት የሚሰጥና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ የአርበኝት ዘመን መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የመጀመሪያው የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎትም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአዲስ አበባ የከተማዋ ክፍሎች በመዘዋወር ለዜጎች ቀልጣፋና ስሉጥ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት ሰጪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዜጎች የሚገባቸውን የመንግሥት አገልግሎት ግልፅና ቀልጣፋ ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው።

ከአገልግሎት ሰጪዎቹ መካከል ዘውዱ አምሳሉ፤ ወቅቱ የሚጠይቀው የዘመኑ አርበኝነት ህዝብን በቅንነት፣ በታማንነትና ታታሪነት ማገልገል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎቱም ዜጎች በመንግሥት አገልግሎት የሚገጥማቸውን መጉላላት በማስቀረት ቅርብና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት የሚያስገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ታላቅ ኩራትና ደስታ የሚቸር የአርበኝነት መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

የሚሰጡት ቀልጣፋና ግልፅ አገልግሎትም የህዝብና መንግሥትን መተማመን በማጠናከር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ለመዲናዋ ነዋሪዎች የተሳለጠ አገልግሎት በማቅረብ ለመጭው ትውልድ አርዓያ የሚሆን አሻራ እያሳረፉ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ሌላኛው አገልግሎት ሰጪ ኤፍሬም አሰፋ በበኩላቸው፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ተገልጋዮች የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።


 

በዘመኑ የልማት አርበኝነት ጉዞም በተሰማሩበት ሙያ ዜጎች የሚፈልጉትን የመንግሥት አገልግሎት በግልፅና ቀልጣፋ አሰራር እየሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለመዲናዋ ነዋሪዎች የሚሰጡት የተሳለጠ ሙያዊ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎትም እንግልትን በማስቀረት እርካታን የሚሰጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመጀመሪያ ዙር ሠራተኛ በመሆኔ እጅግ ደስታ ይሰማኛል ያሉት ደግሞ የማዕከሉ አገልግሎት ሰጪ ጫልቱ ታደሰ ናቸው።


 

ተገልጋዮች ተገልግለው ሲመለሱ የሚሰማቸው ደስታም የአገልግሎት እርካታን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ 150 የመንግሥት ተቋማት በዲጂታል ሥርዓት እየቀረቡ ሲሆን በመጀመሪያው የመሶብ አንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎትም ስምንት ተቋማት አገልግሎት እየተሰጡ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም