በዞኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተቀናጀ የድጋፍና የክትትል ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተቀናጀ የድጋፍና የክትትል ሥራ እየተከናወነ ነው
ገንዳውኃ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተቀናጀ የድጋፍና የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው የብሔራዊና ክልላዊ ፈተናዎችን ቅድመ ዝግጅት በማስመልከት የንቅናቄ መድረክ በገንዳ ውኃ ከተማ ዛሬ አካሄዷል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አያና በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በዞኑ የተማሪዎችን የፈተና ውጤት ለማሻሻል የተቀናጁ የድጋፍና የክትትል ሥራዎች እየተካሔዱ ይገኛል።
በተለይም የ12ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተናው ብቁ እንዲሆኑ የሞዴል ፈተናና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመማር ማስተማሩ ከሚደረግላቸው ድጋፍ በተጨማሪም ተፈታኞቹ የስነ-ልቦና ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችላቸው ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ቤተመጽሐፍቶችን ክፍት በማድረግ ተፈታኞቹ በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያጠኑና በቡድን እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በዘንድሮው ፈተና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልም ትምህርት ቤቶች የአካባቢያቸውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
በገንዳውኃ ከተማ የቁጥር 2- 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ማስረሻ መኮንን በበኩላቸው፤ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከወላጆች ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት ውጭም በትምህርት ቤቱ ተገኝተው ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረግን ነው ብለዋል።
የመተማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መንገሻ ብርሃን እንዳሉት፤በተያዘው ዓመት አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችን በማስገንባት በተለይም ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።
የፈተና ዝግጅቱና የድጋፍ ስራው እስከ ፈተናው እለት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።