ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማህበሩ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ወጣቶች ማህበር አስታወቀ። 

የጋምቤላ ክልል ወጣቶች ማህበር ያሉትን አደረጃጀቶች በማስተባበር ዘንድሮ ለሚካሄደው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ሰለሞን አሰፋ እንደገለፀው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት የሚጥል ነው።

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመሰረተ መንግስት ደግሞ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚኖረው ጠቅሰው  ይህም ለዜጎች የጋራ እድገትና ልማት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማህበሩ ሌሎች የሲቪል ማህበራትና የወጣቶች አደረጃጀቶች ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ህዝቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎች በአግባቡ በመረዳት በቀጣይ ለሀገሪቱ የሚጠቅም ፓርቲ እንዲመርጡ ማህበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ማህበሩ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉት አደረጃጀቶቹ በመጠቀም ህዝቡ ህገ-መንግስታዊ መብቱን በመጠቀም በጠቅላላ ምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ግንዛቤ እየፈጠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የሲቪል ማህበራትም ጠቅላላ ምርጫው ነፃ፣ ፍትኃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲከናወን ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ወጣት ሰለሞን ገልጿል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም