ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች የድርሻቸውን ይወጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች የድርሻቸውን ይወጣሉ
ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 30/2018(ኢዜአ)፡-ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ አባሎቻቸው የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የሲዳማ ክልል የሴቶች እና የወጣቶች አደረጃጀቶች ገለጹ።
ኢዜአ በሀዋሳ ከተማ ያነጋገራቸው የክልሉ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች እንደገለጹት ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ በተለያየ መንገድ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ ነው፡፡
የክልሉ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት በቃሉ መሰረት እንዳለው ወጣቱ በምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ድምጹን ለፈለገው ፓርቲ እንዲሰጥና ለምርጫው ስኬታማነት የበኩሉን እንዲወጣ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም በክልሉ የማህበሩ አባል የሆኑ ወጣቶች በምርጫው መሳተፍ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ በወቅቱ እንዲወስዱ መደረጉን ገልጿል።
የምርጫ ካርድ መውሰድ ብቻ በቂ አይደለም ያለው ወጣት በቃሉ፣ በድምጽ መስጫው እለትም ድምጻቸውን በነጻነት መስጠት እንዲችሉ የማስገንዘብ ሥራ መሰራቱን ተናግሯል።
ህብረተሰቡ በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ወጣቶች የመቀስቀስና የማስተማር ሥራ ከመስራቱ ባለፈ ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት የበኩሉን እንዲወጣ የማስገንዘብ ስራም መከናወኑን አመልክተዋል።
የክልሉ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ገነት ማርቆስ በበኩላቸው እንዳሉት የክልሉ ሴቶች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ በተሰጠው የግንዛቤ ስልጠና በርካቶች ለመራጭነት ብቁ የሚያደርጋቸውን ካርድ ወስደዋል።
ከዚህ ባለፈ ፌዴሬሽኑን ወክለው በታዛቢነት የሚያገለግሉ 65 ሴቶችን በመመልመል ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር በትብብር ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።
ሴቶች በቤተሰብ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ያነሱት ወይዘሮ ገነት፣ ለምርጫው አሳታፊነትና ሰላማዊነት ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከቤተሰብ ጀምሮ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የማስገንዘብ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ጋማርሳ ዲዳ እንዳለው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከ ወረዳ ባሉ የወጣት አደረጃጀቶች በቅንጅት እየተሰራ ነው።
ወጣቱ በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ እንዲወስድ ተደርጓል ያለው ፕሬዚዳንቱ፣ በካርዱም ይበጀኛል የሚለውን ለመምረጥ ዝግጅት እንዲያደርግ የማስገንዘብ ሥራ መሰራቱን ተናግሯል።