በክልሉ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል
ባህርዳር፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ተደራጅተው በማምረት ላይ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክተር ፍቅረማርያም የኔአባት እንደገለጹት ቢሮው ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ በማስገባትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ተደራጅተው በማምረት ላይ ለሚገኙ 35ሺህ 287 ኢንተርፕራይዞች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በተፈጠረው የገበያ ትስስርም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ግብይት መፈጸሙን ጠቁመው ትስስሩ የተፈጠረው ከተቋማት፣ ከኩባንያዎች፣ ከኢንተርፕራይዝ ለኢንተርፕራይዝና ከሌሎች ጋር ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ትስስር በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በማምረቻውና በአገልግሎት ዘርፎች ሲሆን በውጭ ሀገራት ደግሞ ኦፓል፣ ወርቅ፣ የባህላዊ አልባሳት፣ የባልትና ውጤቶችና ሌሎች ምርቶችን በመላክ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀሪ ወራትም የተጀመረውን የገበያ ትስስር በማጠናከር አዳዲስ ለገበያ የሚሆኑ ሀገራትን በማፈላለግ የኢንተርፕራይዞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በደሴ ከተማ ያሬድና ጓደኞቹ ሚስማር ማምረትና ማከፋፋል ማህበር አስተባባሪ ወጣት ሰለሞን ሞላ እንደገለጸው ሚስማር በማምረት ስራ ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ምርታቸውንም በተመቻቸላቸው የገበያ ትስስር በደሴ ከተማና አካባቢው በማከፋፈል የተሻለ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግሯል።
በ2017 በጀት ዓመት ለ40ሺህ 117 ኢንተርፕራይዞች ከ7 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ምርቶች በውጭና በሀገር ውስጥ ገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉንም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።