በዞኑ በመጪው ክረምት የሚተከሉ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በመጪው ክረምት የሚተከሉ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል
ጭሮ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ከ37 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ገለፀ።
በጽህፈት ቤቱ የቡና እና ቅመማ ቅመም ልማት አስተባባሪ አቶ ኦሉማ በዳኔ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በመጪው ክረምት በዞኑ 13 ወረዳዎች የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
የቡና ዝርያዎቹ አብዛኛውን ከመቻራ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቁ እና በሽታንና ድርቅን በመቋቋም በሄክታር እስከ 17 ኩንታል ምርት የመስጠት አቅም ያላቸው መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት እየተሰራ ሲሆን የአካባቢው አርሶ አደሮችም በክረምቱ ወቅት ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ ጉድጓዶችን ማዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
በዞኑ እስካሁን ከ129 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን አመልክተው በዘንድሮው ዓመት ለተከላ የተዘጋጀው የቡና ችግኝም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ8 ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።
በሚካሄደው የቡና ልማት ስራ ከ232 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የቦኬ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት የቡናና ቅመማ ቅመም ልማት አስተባባሪ አቶ ኢብራሂም ሐሰን በበኩላቸው በወረዳው በዚህ ዓመት 3 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት በቡና ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከቡና ዝርያዎቹ መካከል ቡልቱም የተሰኘውና ከመቻራ ግብርና ምርምር ማእከል የወጣው የቡና ችግኝ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በቦኬ ወረዳ ቦኬ ጥቃ ቀበሌ አርሶ አደር አይሻ መሐመድ እንዳሉት ለቡና ችግኝ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ የስራ ዕድል በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ባለፈም የጫት ምርት ያመርቱበት የነበረውን ሁለት ጥማድ መሬት የቡና ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ነው የገለጹት ።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በቡና ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ ለመሆን መቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ የቀበሌው አርሶ አደር ሞሚና ኢብራሂም ናቸው።
በመጪው ክረምትም ከ500 በላይ ተጨማሪ የቡና ችግኞችን ለመትከል ጉድጓዶችን ማዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።