ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መሰጠት ተጀመረ

ጋምቤላ/አሶሳ ፤ሚያዝያ 30 /2018/ (ኢዜአ) ፡- በጋምቤላ ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ መከላከያ ክትባት ዛሬ በዘመቻ መስጠት መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ‎ለክትባት ዘመቻው ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና መላው ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል።

‎የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ በክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከዛሬ ሚያዘያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የበሽታው መከላከያ ክትባት ቤት ለቤት በዘመቻ መሰጠት ተጀምሯል። 


 

በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ክትባትም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑና ከ196 ሺህ ለሚበልቁ ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ክትባቱን መስጠት ያስፈለገው በተጎራባች ሀገራት ድንበር አካባቢ የበሽታው ምልክት በመታየቱ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ክትባቱንም የክልሉ ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከሌሎች የዘርፉ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት መሆኑን አስረድተዋል። 

በክልሉ ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የክትባት ዘመቻ ከ1 ሺህ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውንም አክለዋል።

በክልሉ ለተጀመረው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ስኬታማነት የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና መላው የክልሉ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በክትባት ማስጀመሪያ መረሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የአጋር አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል። 


 

በተመሳሳይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀምሯል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱልሙኒየም አልበሽር በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ የፖሊዮ በሽታ በአጎራባች ሀገር ሱዳን መከሰቱን ተከትሎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሽታው እንዳይዛመት የቅድመ መከላከል ስራ እየተከናወነ ነው።

በክትባት ዘመቻውም ከ220ሺ በላይ ህፃናት ክትባቱን እንዲወስዱ ለማድረግ ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ክትባቱ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች እና የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ቤት ለቤት እንደሚሰጥ ጠቁመው ህብረተሰቡ ህፃናትን በማስከትብ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

ክትባቱ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት እንደሚሰጥም ታውቋል።

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም