ፓርቲው ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት መሰረት የጣሉ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት መሰረት የጣሉ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጓል
ጎንደር፤ ሚያዚያ 30/2018 (ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት መሰረት የጣሉ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረጉን በጎንደር ከተማ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ፡፡
ፓርቲው በጎንደር ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄዷል።
የምርጫ ቅስቀሳውንና የድጋፍ ሰልፉን የተሳተፉ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እንደገለፁት፤ ምርጫ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ወደፊት የሚመራቸውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በቅስቀሳው የተሳተፉት አቶ ዮሃንስ አንዱአለም እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ በለውጡ ዓመታት ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት መሰረት የጣሉ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን መተግበር ችሏል።፡
ምርጫውን ሰላማዊ፣ ነጻና ተዓማኒ በማድረግ ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ የመራጩ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው እርሳቸውም በምርጫው በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፅጌ ቸኮል በበኩላቸው ለሴቶች መብትና ጥቅም መረጋገጥ የሚሰራውን ፓርቲ ለመምረጥ ራሴን አዘጋጅቻለሁ ብለዋል፡፡
"ምርጫ የሰለጠነ ህዝብ የሚተገብረው የዴሞክራሲ ባህል መገለጫ ነው" ያሉት ወይዘሮ ጽጌ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ አበራ በሪሁን በበኩላቸው ምርጫ የህዝቦች የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የሚያሻግር ሃሳብና ራእይ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ የተጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ለማሳካት እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
በምረጡኝ ቅስቀሳው ስነ-ስርዓት ላይም በጎንደር ከተማ የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።