ቀጥታ፡

በዞኑ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተዋል

ጊምቢ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ በምእራብ ወለጋ ዞን ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታቸው የጎላ ችግኞች መዘጋጀታቸውን  የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ  እንዳሉት  በዞኑ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው  ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ከችግኞቹም መካከል ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታቸው የጎሉ የቡና፣ የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ እና ሌሎች  እንደሚገኙበት አስረድተዋል።  

የችግኝ ተከላው በበጋ ወራት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ለእንስሳት መኖ እንዲውልና ለም አፈር በጎርፍ እንዳይወሰድ ለመከላከል ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል። 


 

ይህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

ችግኞቹን  በበጋ ወራት በተከናወኑ የተለያዩ የእርከን ስፍራዎችና የተመረጡ ቦታዎች ለመትከልም  እስካሁን ከ117  ሚሊዮን በላይ ጉድ ጓዶች ቁፋሮ መከናወኑን አቶ ፍቅሩ ጠቅሰዋል።

ስራውን ለማሳካትም አርሶ አደሩን በማሳተፍ መከናወኑን የጠቀሱት ሀላፊው፤ የግብርና ባለሙያች ድጋፍና ክትትል ስራዎች መጠናከራችውን አንስተዋል።

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ደግሞ የጊምቢ ወረዳ አርሶ አደር ዋኬኔ አምሳሉ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ  ችግኞችን ጽድቀት መጠን ለማሳደግ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን  በመንከባከብ  ከሰውና እንስሳት ንክኪ  መጠበቃቸውን ተናግረዋል። 

ዘንድሮም በመንግስት ከሚለሙት ችግኞች ባለፈ እሳቸው በግላቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን ማፍላታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ባለመስጠታቸው ያጡትን ምርታማነት በሚያካክስ መልኩ  በመጪዉ ክረምት የሚተከሉ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች በብዛት  ማዘጋጀታቸው የገለጹት የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ለሊሳ ኤቢሳ ናቸው። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በተሰራው ስራ በርካታ ጥቅም በማግኘታቸውም ስራውን ለማስቀጠል ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም