የአፍሪካውያን አዲሱ የተፅዕኖ ድምፅ በዓላማ የሚመራ የአህጉሪቱንና የትውልዱን ተስፋና ዕድሎች የሚያሳይ መሆን አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካውያን አዲሱ የተፅዕኖ ድምፅ በዓላማ የሚመራ የአህጉሪቱንና የትውልዱን ተስፋና ዕድሎች የሚያሳይ መሆን አለበት
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ) ፦ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ አህጉራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚወሰድ ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ፡፡
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ(ASMIS-2026) እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ''ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አፍሪካ የራሷን ትርክት በራሷ ለመገንባት፣ የአሕጉሪቱን እምነት የሚያሳድጉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ፣ የአፍሪካን መለያ ለመፍጠር የጋራ ምክክር ይደረግበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ጉባኤው የአህጉሪቱን የዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የፐልስ ኦፍ አፍሪካ መወለድ መነሻ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አሳቢ ራዕይ መሆኑን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ የራሷ ድምጽ እንደሚያስፈልጋትና የራሷን ታሪክ በራሷ ልጆች መተረክ እንዳለባት ባስቀመጡት መሰረት፣ ተቋሙ እውነተኛ አፍሪካዊ ትርክቶችን ለማሰራጨት በግልጽ ተልዕኮ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በታላቅ ፍጥነት እያደገ መሆኑን ጠቅሰው ከ30 በላይ በሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ተደራሽነቱን ማስፋቱንና ተቀባይነትን ማግኘቱን ጠቁመዋል።
"ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው ጉባኤው አህጉራዊ ተፅዕኖን ለማሳደግና ለማነቃቃት ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተዕፅኖ ዘመኑን በዋጀ አዲስ ዕይታ ሊበየን እንደሚገባው በማንሳት፥ ለዚህም በዓላማና በኃላፊነት የሚመራ እንዲሁም ውጤት የሚያመጣ ሊሆን እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል።
የዲጂታል ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካን ትርክት ለመቀየር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የዲጂታል ተጽዕኖን ለማዝናናት ብቻ ሳይሆን ለማስተማር፣ አንድነትን ለማጠናከርና አህጉሪቱን ለመገንባት መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
የሴቶችን መሪነት የሚያጎላና ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት፣ ብዝበዛና በደል የሚቃወም የዲጂታል ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው አብሮነትን፣ የትውልዱን ተስፋና ዕድሎች አጉልተው የሚያሳዩ ትርክቶችን ማስፋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካን ታላቅነትና ባህል በማስተዋወቅ ወጣቱን ትውልድ ለፈጠራና ለልማት ማነቃቃት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ይህንን አዲስ ንቅናቄ የሰው ዘር መገኛ፣ የአፍሪካ መዲና እና የአህጉሪቱ የጽናት ምልክት ከሆነቸው ሀገር-ኢትዮጵያ መጀመር እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ያላቸውን ተቀባይነት በጥበብ፣ በድፍረት እና ለአፍሪካ ባለ ጥልቅ ፍቅር መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ እንዲተርኩ ላደረጉት እገዛና ለአህጉሪቱ እድገት ላላቸው ቁርጠኝነት ታላቅ አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
ለጉባኤው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ለቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ለሌሎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡