የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአህጉሪቱ የባህል አምባሳደርና የአዲሱ ትውልድ ድምፅ መሆን አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአህጉሪቱ የባህል አምባሳደርና የአዲሱ ትውልድ ድምፅ መሆን አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአህጉሪቱ የባህል አምባሳደርና የአዲሱ ትውልድ ድምፅ መሆን እንዳለባቸው የኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመዳ ኦላና ገለጹ።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ''ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ጉባኤ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ጉባኤው ኃላፊነት የሚሰማቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጠናከር፣ ትብብርን ለመፍጠርና የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግብን ለማሳካት ያለመ ነው።
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አፍሪካ የራሷን ትርክት በራሷ ለመገንባት፣ የአህጉሪቱን እምነት የሚያሳድጉ ውጤቶች ለማስመዝገብ እና የአፍሪካን መለያ ለመፍጠር ምክክር ይደረግበታል።
በጉባኤው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ ዜና አገለግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፣ የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
የኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመዳ ኦላና በመድረኩ፤ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ፣ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል የብዝሃ ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻ ናት ብለዋል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤም ስብሰባ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የዲጂታል ንቅናቄ ለመፍጠር የመጀመሪያ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የታሪክ ሃብታም፣ የፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ባለቤት፣ በዲጂታል አብዮት አስደናቂ የለውጥ ምኅዋር ላይ የምትገኝ መሆኗን ተናግረዋል።
የአህጉሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ልጆቿም የመላው አፍሪካ ታሪክ ነጋሪ፣ የባህል አምባሳደር የአዲሱ ትውልድ ድምፅ መሆን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአህጉሪቱን ፈጠራና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማገናኛ ድልድይ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል።
ጉባኤው የአፍሪካ የዲጂታል እንቅስቃሴ ጅማሮ መሆኑን ጠቁመው፤ ግባችን በአፍሪካ ዓለምአቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ማፍራት ነው ብለዋል።