ቀጥታ፡

የክልሉ ወጣቶች ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ እየተወጡ ያሉትን ሃላፊነት ያጠናክራሉ-ኮሚሽኑ

ጂንካ፤ሚያዚያ 30/2018(ኢዜአ) ፡-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ እየተወጡ ያሉትን ሃላፊነት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ የክልሉ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን አመለከተ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ የወጣት ተወካዮች፣ ለወጣት አደረጃጀቶች፣ ለማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጂንካ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች እና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ማርቆስ ማቲዮስ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ የክልሉ ወጣቶች ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ እየተወጡ ያሉትን ሃላፊነት አጠናክረው ሊያስቀጥሉ ይገባል።


 

በክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ መውሰዳቸውንና ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በክልሉ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች የምርጫ ሂደቱን ለመታዘብ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ማግኘታቸውን ጠቁመው ወጣቶች አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ ምርጫው ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በአቅም ግንባታ ስልጠናው የተሳተፉ ወጣቶችም ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንደሚወጡም ገልጸዋል ።

የጂንካ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሀቁ ገዛኸኝ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ  የበለፀገችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻዬን እወጣለሁ ነው ያለው።

የማህበራዊ ሚዲያ አንቂው ፍቃዱ ደገፌ በበኩሉ ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቱ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ በምርጫው እንዲሳተፍ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በመቀስቀስና በማስተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የባስኬቶ ዞን የላስካ ከተማ ነዋሪ ወጣት ታምራት ደጄ በበኩሉ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በመራጭነት፣ በምርጫ ታዛቢነት እና በደንብ አስከባሪነት እንዲሳተፉ በማስተባበር ለምርጫው ስኬታማነት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም አረጋግጧል።


 

ወጣት አንለይ አካልቆ በበኩሏ ካርድ ከመውሰድ አንስቶ ለሴቶች ግንዛቤ በመፍጠር በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ የማስተባበር ስራ እየሰራች እንዳለች ገልፃለች።

ግንቦት 24 በሚካሄደው ምርጫ ለሀገሪቱ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ በጉጉት እየጠበቀች መሆኑንም ጠቁማለች።

በአቅም ግንባታ ስልጠናው በምርጫው የወጣቶች ሚና፣ የምርጫ ስነ-ምግባርና ህጎች ዙሪያ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

በአቅም ግንባታ ስልጠናው በክልሉ ከሚገኙ ከሁሉም ዞኖች የተወጣጡ ወጣቶች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም