ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን አሳድጎታል

አርባ ምንጭ ፤ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ) ፡-የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር  ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን በማሳደግ ትርጉም ባለው መልኩ ህይወታችንን ቀይሮታል ሲሉ በጋሞ ዞን የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አመጋገባቸውን ከመቀየሩ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን አልቆታል።

በዚህም መርሃ ግብሩ ህይወታቸውን ትርጉም ባለው መንገድ እንደቀየረም ተሳታፊዎቹ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በዞኑ በምዕራብ አባያ ወረዳ አንኮበር ቀበሌ "የጦይሎ ንብ አንቢዎች ማህበር ሰብሳቢ ደሰ ኡታሎ፤ የማህበሩ አባላት በንብ ማነብ ስራ ላይ በመሰማራት ከማር ሽያጭ ጥሪት እንዲያፈሩ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አባላቱ በሚያገኙት ገቢ ከመኖሪያ ቤት ግንባታ ጀምሮ የቤት ቁሳቁሶችን በማሟላትና ልጆቻቸውን በማስተማር ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

መንግስት ባመቻቸላቸው 19 ሄክታር ደን ውስጥ የንብ ማነብ ተግባራትን ከማከናወን ጎን ለጎን የደን ጥበቃ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማህበሩ  በ102 ዘመናዊና በ2 ሺህ 530 ባህላዊ ቀፎዎች ማር በማምረት በየዓመቱ ከ100 ሺህ ብር በላይ እየቆጠቡ ይገኛሉ።


 

በቦረዳ ወረዳ መሳ ቡንታዛ ቀበሌ የአንድነት የዶሮ አርቢ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት መስፍን ደነቀ በበኩላቸው፤ በመርሃ ግብሩ ያረቧቸውን ዶሮዎች ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ የወረዳው ነዋሪዎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ እያገዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቦረዳ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደጉ ማጃ ናቸው።

መርሃ ግብሩ በህብረተሰቡ መካከል መልካም የሆነ መነቃቃትና የስራ ባህልን በመፍጠር ከድህነት እንዲላቀቁ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው  ብለዋል።


 

የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ካልሳ በበኩላቸው፤ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ በዞኑ በ14 ወረዳዎችና በ6 ከተማ አስተዳደሮች እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሁሉም መዋቅሮች የወተት፣ የስጋ፣ የዶሮ፣ የማር እና የዓሣ መንደሮች የተደራጁ ሲሆን በዝርያ ማሻሻልና በጤና አገልግሎት የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም