ቀጥታ፡

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት ኢንሹራንስ ሽፋንን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፡- በአርብቶ  አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ  የእንስሳት ኢንሹራንስ ሽፋንን በማሳደግ  የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ትኩረት መሰጠቱን የኦሮሚያ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሮባ ቱርጬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በክልሉ የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  የእንስሳት ሀብት  የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን የማጠናከር ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በተጨማሪም ፣የመኖ እቅርቦትና የውሃ አማራጮችን ማስፋት፣የእንስሳት ቁጥርን የማመጣጠን እና የክትባት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ነው የገለጹት ።

የእንስሳት እንሹራንስ ሽፋንን ተደራሽ በማድረግም በድርቅ ወቅት ለመኖ ፣ የውሃ አቅርቦት፣ ለእንስሳት መድሀኒትና ለጤና አገልግሎት  እንዲያውል  እየተሰራ ነው  ብለዋል።

በዚህም 130 ሺህ በላይ  አርብቶ አደሮች የኢንሹራንስ አባል መሆናቸውን የገለጹት ምክትል የቢሮ ኃላፊው  ይህም   የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት  በተጨባጭ ማረጋገጥ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም  የኢንሹራንሱ አባል ለሆኑ አርብቶ አደሮች  ለመኖ  እና ውሃ አቅርቦት፤ ለእንስሳት ጤና መጠበቂያ የሚሆን  ከ930 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንሹራንስ መከፈሉንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋምና አርብቶ አደሩ ከእንስሳት ሀብቱ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ የኢንሹራንስ ሽፋኑ  ተደራሽነት  ለማስፋት  ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም