ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለዚምባቡዌ ባለሃብቶች የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ መነቃቃት እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለዚምባቡዌ ባለሃብቶች የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑን በዚምባቡዌ፣ በዛምቢያና በሞሪሽየስ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ ረሽድ መሀመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያና ዚምባቡዌን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በማጠናከር በኢኮኖሚ ግንኙነት ዘርፍ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ በፖለቲካና በፓን-አፍሪካኒዝም ዕሳቤ የተመሠረተ ጠንካራና ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

የቀድሞዋ ደቡብ ሮዴዢያ የአሁኗ ዚምባቡዌ .. 1960ዎቹ እስከ 1980 ድረስ ከብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ባደረገችው እልህ አስጨራሽ የነፃነት ተጋድሎ የኢትዮጵያ ድጋፍ በታሪክ ይወሳል።

የዚምባቡዌ የነፃነት ተጋድሎና የኢትዮጵያ ድጋፍም በታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም የተፃፈ የአፍሪካውያን አህጉራዊ አንድነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኢትዮጵያም በዚምባቡዊ የነፃነት ተጋድሎ ዘመንም የቅኝ አገዛዝ ስርዓትን በፓን-አፍሪካኒዝም ዕሳቤን የማይተካ የገንዘብና ወታደራዊ ስልጠና ድጋፍ በመስጠት ግንባር ቀደም ሚና ተወጥታለች።

የሀገራቱ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረክ የአህጉሪቱን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠብቁ የጋራ አቋሞችን በዓለም አደባባይ በማንፀባረቅ የሚተባበሩ ጠንካራ ወዳጅ ሀገራት ለመሆን በቅተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሀገራቱ በግብርና፣ ቱሪዝም፣ በአቪዬሽን ዘርፍና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በደምና በጋራ ነፃነት የተመሰረተ አጋርነታቸውን እያስቀጠሉ ይገኛሉ።

አምባሳደር ረሽድ መሐመድ በቨርቿል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮ-ዚምባቡዌ ግንኙነት በቅኝ ግዛት ዘመን የነፃነት ተጋድሎ ወቅት የተጀመረና በታሪካዊ ወዳጅነት የተመሠረተ ነው።

ለአብነትም ዚምባቡዌ የቅኝ ግዛት ነፃነቷን በተቀዳጀች ማግስት .. 1980ዎቹ ሀገራቱ በሀራሬና አዲስ አበባ ኤምባሲዎቻቸውን በመክፈት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሀገራቱ ታሪካዊ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም በቅርቡ የኢትዮጵያውያን የቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪዎች በዚምባቡዌ ዓለምአቀፍ የንግድ ትርዒት በመሳተፍ የንግድ ምርታቸውን በማስዋወቅ የንግድ ትስስር መፍጠር እንደቻሉ አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አስቻይ የልማት ምኅዳር ለዚምባቡዌ አልሚ ባለሃብቶች በማስተዋወቅ የተከናወኑ ተግባራትም በንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን መፈረሟና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባል መሆኗ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

በዚምባቡዌ ዓለምአቀፍ የንግድ ትርዒት የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን አምራቾችን የጉዞና አገልግሎት ወጪ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እንዲሸፈን መደረጉንም ገልጸዋል።

በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የዳኞች ሹመትም ኢትዮጵያ በኮሜሳ የፍትሕ ፍርድ ቤት የሚገባትን ውክልና ማግኘቷን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በሶስት የዚምባቡዌ ከተሞች በሳምንት 23 በረራዎችን በማድረግ የሀገራቱን የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እያጎለበተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም