በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ በመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሣታፊዎች ገለጹ፡፡
የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ በደመቀ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ /pulse of Africa/ ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ጉባኤ ነው፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እና የኮሪደር ልማቶችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ታዋቂው ጋናዊ የይዘት ፈጣሪ በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር (ዎዴ ማያ) በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ ለመላው አፍሪካ አህጉር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በሀገሪቱ የታየውን ለውጥ ለዓለም ለማሳየት በድጋሚ መምጣቱን ጠቅሶ እ.ኤ.አ በ2017 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከነበረበት ወቅት ጋር ሲነፃፀር አሁን በ2025 እና 2026 እያያት ያለችው ኢትዮጵያ በአዲስ ገጽታና ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ መስክሯል፡፡
በተለይም በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ ሰፋፊ መንገዶች፣ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ለሀገሪቱ ዕድገት ማሳያና እጅግ የሚደነቁ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
ይህ ስኬት ለአህጉሪቱ ብልጽግና ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ መላው አፍሪካ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ሊቀስም ይገባል ብሏል።
ከናይጄሪያ የመጣው የይዘት ፈጣሪ ኦዲናካ በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ቀዳሚ መሆኗን መመልከቱን ተናግሯል፡፡
ቴክኖሎጂው ዓለምን እየተቆጣጠረ ባለበት በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ለዘርፉ የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጿል።
ይህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታየው ስኬት ግለሰቦችንም ሆነ ሀገርን ለማልማት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጉዞ የሚደነቅ ነው ብሏል፡፡
ከሌሴቶ የመጣው የይዘት ፈጣሪ ቴኤሎ ሉዓሎ እንዳለውም፤ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት አለመገዛቷና የራሷ የሆነ የቀን መቁጠሪያ ባለቤት መሆኗ ለአፍሪካውያን ታላቅ ኩራትና የማንነት መገለጫ መሆኑን ተናግሯል።
የታየው የሀገሪቱ የበለፀገ ታሪክና ጠንካራ ባህል ሌሎች ሀገራትም የራሳቸውን ቱባ ባህል ጠብቀው እንዲቆዩ ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲል ገልጿል፡፡