በክልሉ የተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከችግርና እንግልት ታድጎናል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከችግርና እንግልት ታድጎናል
ሐረር፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እናቶች ገለጹ።
በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረጋውያንንና የአቅመ ደካማ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመቅረፍ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ነው።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው የታደሰላቸው ወይዘሮ የሺ ደመቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፣በክረምት ዶፍና በበጋ ንፋስ ያዘመመና ለብልሽት ተጋልጦ የነበረው የመኖሪያ ቤታቸው በመታደሱ ከስጋት ተገላግለዋል።
ለችግራቸው ፈጣን ምላሽ የሰጡ የመንግስት አካላትንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችንም አመስግነዋል።
በበጎ ፈቃደኞች የመኖሪያ ቤት ተገንብቶ ከተሰጣቸው አንዷ የአምስት ልጆች እናት ወይዘሮ አሻ ኡስማኢል ይገኙበታል።
የቤት ባለቤት መሆናቸው ልጆቻቸውን በአግባቡ ለማሳደግና በትምህርታቸውም በርትተው እንዲያድጉ እንደሚያግዛቸው ያስረዳሉ።
የተደረገላቸው ድጋፍ በቀጣይ ሰርተው እራሳቸውን ለመለወጥ ብርታት ከመሆኑም በላይ አጋዥ ወገን እንዳላችው ያረጋገጡበትና ሰርተው ለመለወጥ ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በአንድ ክፍል ውስጥ ባልተመቻቸ ሁኔታ ይኖሩበት የነበረን ቤት በማደስ ምቹ ቤትን በመረከባቸው መደሰታቸውን የሚነግሩን ደግሞ ወይዘሮ ፈቲያ መሀመድ ናቸው።
ከመኖሪያ ቤቱ ባለፈ ወደ ስራ በመግባት ራሳቸውን እንዲችሉ የተመቻቹላቸው የስራ እድልም ጠንክረው ለመስራት ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረጋውያንና የአቅመ ደካማ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመቅረፍ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ተናግረዋል።
ቢሮው አክሎም፣ ይህ የበጎ አድራጎት ተግባር በዜጎች መካከል ያለውን መረዳዳት ከማጠናከሩ ባለፈ የወገኖቻችንን እንግልት በእጅጉ ቀንሷል ብሏል።
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ረምዚያ አብዱልወሃብ እንዳሉት በክልሉ በበጀት ዓመቱ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 220 ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት በክልሉ ተከናውነዋል።
ከእነዚህ ውስጥም የ154 የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት በመገንባትና በማደስ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካማ ዜጎች ማስረከብ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከሰሞኑም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና እና ተጠሪ ተቋማቱ በክልሉ ያስገናቡትን 12 የአቅመ ደካማ ወገኖች መኖሪያ ቤቶችን አጠናቀው ማስረከባቸውን ጠቁመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራቱም በበጋም ሆነ በክረምት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሰተዳድር ኦርዲን በድሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ያስገነባውን መኖሪያ ቤት ባስረከበቡት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎችን ማከናወኑን መናገራቸው ይታወሳል።