ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት እያደገ ነው

ደሴ፤ ሚያዚያ 30/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ወሎ ዞን የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት እያደገ መሆኑን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በዞኑ 331 አነስተኛ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች እና 5 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ለአገልገሎት መብቃታቸው ታውቋል። 

በዚህም የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት እያደገ መሆኑን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ጽጌ ገልጸዋል። 


 

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በመንግስት ጥረት፣ በህብረተሰቡና በአጋር አካላት ትብብር የተከናወነ መሆኑን አንስተው፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ149 ሺህ 964 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

በግንባታ ላይ የሚገኙ ሌሎች 138 አነስተኛ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣  በቀሪ ወራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። 

የዞኑ ነዋሪዎች ወይዘሮ ሀዋ ፋሪስ  እና አቶ ሰይድ መሃመድ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ብዙ እንግልትና ወጪ ይገጥማቸው እንደነበር አንስተው፣ በመንግስት ጥረትና በህብረተሰቡ ትብብር በተሰራው ሥራ በአቅራቢያችን ውሃ ማግኘት ችለናል፤ ለዚህም እናመሰግናለን ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ከ181 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም