በምዕራብ ሸዋ እና ሐረርጌ ዞኖች በበጋ ስንዴ ከለማው ማሳ ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ እና ሐረርጌ ዞኖች በበጋ ስንዴ ከለማው ማሳ ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ
አምቦ/ጭሮ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ እና ሐረርጌ ዞኖች በዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የየዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ ልማት ባለሙያ ቢቂላ ጉቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ በምግብ ራሱን ለማስቻል ለበጋ መስኖ ልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወቅት 388 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴን በማልማት ከ16 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ ቀድሞ የደረሰውን ሰብል እየሰበሰበ ሲሆን የሰው ኃይልና ሜካናይዜሽንን በማቀናጀት መከናወኑን ገልፀዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በበጋ መስኖ ስንዴ ከተሸፈነው 253 ሺህ ሄክታር ከሚሆን ማሳ ላይ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
ዘንድሮ የተሻለ ምርት መሰብሰቡን አመልክተው ለዚህም አርሶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የግብርና ግብዓቶችን በአግባቡ እንዲጠቀም በመደረጉ ነው ብለዋል።
ቀሪው የበጋ ስንዴ ምርትም ከብክነት በጸዳ መልኩ የመሰብሰቡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን የወልመራ ወረዳ አርሶ አደር ብርሀኑ ተሾመ በበኩላቸው፤ በበጋ ስንዴ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ከአራት ዓመት ወዲህ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት የመስኖ ውሃ በመጠቀም ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳ 40 ኩንታል የስንዴ ምርት መሰብሰባቸውን ጠቁመዋል።
በኩታ ገጠም ስነ-ዘዴ በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ገላና ሰቦቃ ናቸው።
በተመሳሳይም በክልሉ ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቋል።
በጽህፈት ቤቱ የስንዴ ልማት አስተባባሪ አቶ ሀቢብ አብዱልከሪም እንዳስታወቁት፤ በዞኑ 15 ወረዳዎች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 50 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ተሳትፈው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምርት ማሰባሰብ ሂደቱ በሜካናይዜሽን መታገዙን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ምርቱ ሙሉ በሙሉ ተሰብስቦ መግባቱን አስታውቀዋል።