ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት ህብረተሰቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጓል

ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የክልሉን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ህብረተሰቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የክልሉ አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኒሼቲቭ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስና የአካባቢን ሥነ ምህዳር በማስተካከል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።


 

የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ ተስፋሁን አለምነህ ለኢዜአ እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በክልሉ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ የደን ሽፋን ላይ አበረታች ለውጥ ታይቷል።

ለዚህም ባለፉት ዓመታት በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች የክልሉን የደን ሽፋን ቀደም ሲል ከነበረበት 13 ነጥብ 8 በመቶ በአሁኑ ወቅት ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ማሳደጋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።


 

ልማቱ የተራቆቱ አካባቢዎች በአረንጓዴ እንዲሸፈኑ፣ የአፈር መሸርሸር እንዲቀርና ለምነቱ እንዲጨምር እንዲሁም የከርሰና የገጸ ምድር ውሃ እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በለሙ አካባቢዎች አርሶ አደሩ የእንስሳት መኖን ጨምሮ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ቸግኞችን በመትከል ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተዋል።

በተለይ መርሀ ግብሩ በእንስሳት እርባታ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በወተት ልማትና በንብ ማነብ ሥራ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው ያስታወቁት።


 

በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት በበኩላቸው፣ በዘንድሮ ክረምትም የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራን አጠናከሮ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

እስካሁንም ዘንድሮ ከሚተከለው አጠቃላይ ችግኝ 94 በመቶ የሚሆነው ተፈልቶ ለተከላ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ ለችግኝ ተከላም ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከሉ አጠቃላይ ችግኞች ውስጥ 86 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን በመጀመሪያ ዙር በተካሄደ ቆጠራ መረጋገጡን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም