በክልሉ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎን የማጎልበት ተግባራት ይጠናከራሉ-ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎን የማጎልበት ተግባራት ይጠናከራሉ-ፌዴሬሽኑ
ሆሳዕና ፤ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለፀ።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ፋጡማ ተሰማ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ፌዴሬሽኑ የክልሉ ሴቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል።
በክልሉ የምርጫ ሂደቱን አካታችና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ 3 ሺህ 500 የምርጫ ታዛቢዎችን የመለየትና የማሰልጠን ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የጎዳና ላይ ሩጫን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ማህበረሰቡ በወሰደው ካርድ ድምፅ የመስጠት መብቱን እንዲጠቀም ተገቢ ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ሴቶች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የክልሉ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ፎዚያ መሀመድ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ ለምርጫ ታዛቢነት የተለዩ ሴቶችን ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የታዛቢነት መለያ እንዲሰጣቸው ተደርጓል ብለዋል።
በምርጫ ሂደቱ የሴቶችን የመምረጥና የመመረጥ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ተግባሩ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
በሆሳዕና ከተማ የሴቶች ማህበር አባል ወይዘሮ ትዕግስት ፍርዱ እንደገለፁት ፤የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒና ፍትሀዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የታዛቢነት ስልጠና ወስደዋል።
የወሰዱትን ስልጠና መነሻ በማድረግ ማህበረሰቡ በወሰደው ካርድ ድምፅ የመስጠት መብቱን እንዲጠቀም የሚያስችል ግንዛቤ እየፈጠሩ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡