ቀጥታ፡

በዞኑ በመኸር ወቅት ከ484 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ሰብል ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጊምቢ፣ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ) ፡-በምእራብ ወለጋ  ዞን በመኸር ወቅት ከ484 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና  ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝዕርት ልማትና እጽዋት ጥበቃ ቡድን መሪ ወይዘሮ እጅጋየው አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ  በ2018/19 ምርት ዘመን መኸር ወቅት 484 ሺህ 76 ሄክታር መሬት  አርሶ በተለያዩ ሰብሎች ዘር ለመሸፈን የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ።

የመኸር እርሻውን ውጤታማ ለማድረግ  ለኩታ ገጠም እርሻና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በምርት ወቅቱ በቆሎ፣ ገብስ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች እንደሚለሙ ጠቁመው ለምርት ማሳደጊያ የሚሆን  ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ  ለአርሶ አደሩ  እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርት ወቅቱ የተሻለ ምርት ለማግኘት በአሲድ የተጎዱ መሬቶችን በኖራ የማከም ስራ  እየተከናወነ  መሆኑንም አመልክተዋል።

እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ በምርት ወቅቱ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በመኸር አዝመራው  የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በወቅቱ በማግኘታቸው መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጊምቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቱሉ አኩማ  ናቸው።

በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን በግብርና ባለሙያዎች  ምክር በመታገዝ  በኖራ በማከም ጭምር ለዘር ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።

ሌላው የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር እንዳለ  ቶላ፣ በበኩላቸው  መሬታቸውን  በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመሩ ወዲህ የሚያገኙት ምርት እያደገ በመምጣቱ በዘንድሮ መኸርም ተግባሩን ማስቀጠላቸውን ገልጸዋል ።

በመኸር ልማቱ  ምርታማነታቸው የጨመሩ  የበቆሎና ስንዴ ምርጥ ዘር በማግኘታቸው ስራቸውን  ለማሳካት   እየተጉ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም