ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ95ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ95 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ወደ ስራ መገባቱን የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የከተማ ግብርና ዕህፈት ቤት ሀላፊ ደጀኔ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው በመኸር እርሻ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

የመኸር እርሻውን ውጤታማ ለማድረግ የስንዴ፣ ጤፍ፣ የገብስና ሌሎች ምርጥ ዘሮችንና ማዳበሪያን ለአርሶ አደሮች በወቅቱ የማድረስና የግብርና ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው የመኸር እርሻ 47ሺህ 751 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 95ሺህ 500 ሄክታር መሬት በማልማት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

የመኸር እርሻ ልማቱን ለማሳካትም አሲዳማ መሬቶችን በኖራ የማከምና ለሜካናይዜሽን ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም የግብርና ግብዓት አቅርቦት በዩኒየኖችና ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦትንም ለማሳደግ የዘር ብዜት ከሚያቀርቡ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የአፈር ለምነትን ለመጨመርም የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ያነሱት ሀላፊው፣ አሲዳማ መሬት ለማከም ደግሞ ከ2ሺህ 400 ኩንታል በላይ ኖራ መቅረቡን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም