በምርጫው የዜጎች ተሳትፎን ለማሳደግና ሂደቱም ሠላማዊና ተአማኒ እንዲሆን የድርሻችንን እየተወጣን ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው የዜጎች ተሳትፎን ለማሳደግና ሂደቱም ሠላማዊና ተአማኒ እንዲሆን የድርሻችንን እየተወጣን ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች
ሀዋሳ፤ሚያዚያ 30/2018(ኢዜአ):-በጠቅላላ ምርጫው የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ለማሳደግና ሂደቱም ሠላማዊና ተአማኒ እንዲሆን የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለፁ።
በሀዋሳና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በንቃት በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማስገንዘብ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተባባሪ አቶ ማስረሻ ክብረት እንዳሉት፣ በሲዳማ ክልል ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጠቅላላ ምርጫው ዜጎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው።
በዚህም የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ለማሳደግ እና ሂደቱ ሠላማዊና ተአማኒ እንዲሆን ለማስቻል ዜጎችን በማንቃት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።
ድርጅቶቹ ለመራጮች ትምህርት ሲሰጡ ሕግና አዋጅን ተከትሎ ከመስራት ባለፈ ምርጫው አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።
በምርጫው ሂደት ቁልፍ ሚና ካላቸው የመንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት የምርጫው ሂደት ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን ድርጅቶቹ እየሰሩ መሆኑንም አቶ ማስረሻ ገልጸዋል፡፡
የእስካሁኑ የምርጫ ሂደትም አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ሠላማዊ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሪሰረክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን አስፈፃሚ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም በላቸው በበኩላቸው እንዳሉት በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ለመራጩ ህዝብ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በምርጫ ሂደትና ተሳትፎ ላይ በቂ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ወጣቶቹም ወደየመጡበት አካባቢ በመሄድ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየሰሩ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በሲዳማ ባህል “ዋሬ” የተሰኘውን የማህበራዊ መስተጋብር ማጠናከሪያ መድረክ በመጠቀም የመራጮች ትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በእስካሁኑ ሂደትም ከ100 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
ሥልጠና ከወሰዱ ወጣቶች መካከል የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አለማየሁ አበራ ምርጫ የነገ መሪን በነጻነት ለመምረጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሂደት መሆኑን ተናግሯል፡፡
በስልጠና ያገኘውን ግንዛቤ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን የተለያዩ ባህላዊ መስተጋብርን በመጠቀም ህብረተሰቡን የማስተማር ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጿል።
የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ዘሪሁን ሰለሞን በበኩሉ ስለ ምርጫ ሂደት እና ስለ ምርጫ ቦርዱ አሰራር ግንዛቤ በሥልጠና ማግኘት መቻሉን ተናግሯል።
ያገኘውን እውቀት ለአካባቢው ህብረተሰብ በማካፈል የምርጫ ካርድ እንዲወስዱና አንድ ድምጽ ትልቅ ዋጋ እንዳለው እንዲረዱ ማድረጉን ገልጿል።