ቀጥታ፡

የከፍተኛ ደረጃ የፓናል ውይይቶች በአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እና በኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ የጋራ ትብብር የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን በባለቤትነት መምራትን ያለመ ነው።

በታሪካዊው ሁነት ላይ ጉባኤው ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ግለሰቦቹ በድምሩ 321 ሚሊየን የሚጠጋ ተከታይ አላቸው።

ከዚህ ባለፈ በድምሩ 150 ሚሊየን ተከታዮች ያዓቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎችም በጉባኤው አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ ይካፈላሉ።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በመጀመሪያ ቀን ውሏቸው በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ እና የጉለሌ እንጀራ ማምረቻን ጎብኝተዋል።

በአዲስ አበባ የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና የኮሪደር ልማቶችን እንዲሁም ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል አዲስ አበባ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ የአፍሪካን ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደገና የመቅረጽ ውጥን ይዟል።

በዛሬው የጉባኤ ውሎ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በመጠቀም የይዘት ፈጣሪነት የወደፊት ሁኔታ፣ የአፍሪካ አዎንታዊ ገጽታን መገንባት እና የዲጂታል ተጽዕኖን ከአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ጋር ማጣጣም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሶስት የከፍተኛ ደረጃ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።

ጉባኤው በችግሮች ላይ ብቻ በማተኮር የሚሰሩ ዘገባዎችን በእውነተኛ የአፍሪካ የዕድገት ታሪኮች ለመተካት ያለመ ስትራቴጂካዊ ተነሳሽነት መሆኑ ተመልክቷል።

በተጨማሪም ጉባኤው በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄዱ፣ አፍሪካ የራሷን ታሪክ ራሷ መተረክ ለጀመረችበት አዲስ ዘመን ትልቅ ትርጉም እንዲሰጠው አድርጓል።

ከ470 ሚሊየን በላይ የዲጂታል ተከታዮች አይኖች በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ላይ አርፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም