የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዳግም ውልደት አብስሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዳግም ውልደት አብስሯል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ በሚዲያ ዘርፍ የፈጠረው አስቻይ ምኅዳር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዳግም ውልደት ማብሰሩን የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ በመገናኛ ብዙኅን የለውጥ እርምጃና ቀጣይ የትኩረት መስክ ላይ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው መድረክ የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ተቋሙን ከሀገራዊ ለውጡ በፊትና በለውጡ ሂደት ያለፈባቸውንና የቀጣይ ትኩረት መስኮችን አብራርተዋል።
በ1934 የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፉት ስምንት አስርት ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ማለፉን ጠቅሰው፥ እስከ መፍረስ ደርሶ እንደነበርም አስታውሰዋል።
የሥራ ባህል ድክመት፣ የቴክኖሎጂ ክፍተት፣ የብዝሃነት እጦትና የአሰራር ክፍተቶች ተቋሙ በበርካታ ውጣ ውረድ እንዲያልፍ ያደረጉ ዐበይት ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡም ኢዜአ በዕሳቤና የተቋም ግንባታ፣ በውስጣዊና ውጫዊ ትስስር፣ በሕግ፣ በአደረጃጀትና በአሠራር ሪፎርም ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥም የኢዜአን ዳግም ውልደት በማብሰር የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹን ከ14 ወደ 38 በማሳደግ የተደራሽነት አድማሱን ከምንም ወደ 700 ወረዳዎች ማድረስ እንዳስቻለው ተናግረዋል።
በቋንቋ ብዝሃነትም ከ2 ወደ 8 የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋ ማሳደጉን በማንሳት፥ ከ22 ሀገራት 30 ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር አጋርነትን ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የብሪክስ ሚዲያ ፕሬዚዲየም አባል ሆኖ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት።
በቴክኖሎጂም በሁሉም የማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ዜና እና ዜና ነክ ጉዳዮችን በቀን እስከ 250 ይዘቶችን በማመንጨት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ፣ ብሔራዊ መግባባት በሚፈጥሩና የሀገር ገጽታ በሚገነቡ ጉዳዮች ላይ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እነዚህ ሀገራዊና ተቋማዊ የአሰራር ማሻሻያዎችም አንጋፋውን ተቋም ዘመኑን በዋጀ፣ እሳቤ፣ ቴክኖሎጂና የሰው ሃይል እንዲመራ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪና አስተማማኝ የዜና ምንጭ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካን ትርክት የሚቀርፅና ድምጿን የሚያሰማ የራሷ ፓን አፍሪካዊ ሚዲያ ያስፈልጋል ያሉትን ሀሳብ መነሻ በማድረግም የአፍሪካን ትርክት መገንቢያ የሆነው የፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) ሚዲያ እውን መሆኑን ገልጸዋል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) ከምስረታው ማግስት የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚዲያ አዋርድን በስኬት ማስተናገድ እንደቻለ አስታውሰዋል።
ሚዲያው ከ31 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የአህጉሪቷ ልጆች የሚሳተፉበትን የመጀመሪያውን የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ የተቋቋመለትን ዓላማ ወደ ተግባር እየለወጠ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
በቀጣይ የትኩረት መስኮችም ኢዜአንና ፐልስ ኦፍ አፍሪካን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ በማድረግ አህጉራዊ ተቋምነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ብሔራዊ መግባባትን ማዕከል በማድረግ ጠንካራና ወሳኝ የይዘት ፈጠራ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።