የለውጡ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት ያገጥሟቸው የነበሩ ተግዳሮች መፍታት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት ያገጥሟቸው የነበሩ ተግዳሮች መፍታት አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት ይገጥሟቸው የነበሩ ተግዳሮቶችን መፍታት ማስቻሉን የመገናኛ ብዙሃን የሥራ ሀላፊዎች ገለጹ።
መንግስት ያከናወናቸው አጠቃላይ ማሻሻያዎች የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን ገጽታ ከመሰረቱ በመቀየር ለዕድገት፣ ለአካታችነት እና ለሙያዊ ብቃት መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የህትመት ዘርፍ የለውጡ መንግሥት ትልቅ ትኩረት በመስጠት ሪፎርም ካደረገባቸው ዘርፎች አንዱ ነው።
በተለይም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያጋጠመውን ተቋማዊ ውስንነቶች በመለየት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሪፎርሙ ተቀዳሚ እርምጃ እንደነበር አስታውሰዋል።
የይዘት ጥራትና ብዝሀነትን ማስፋት፣ ሚዲያውን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ ተደራሽነትና ስርጭትን ማሳደግ እንዲሁም ተገቢ አደረጃጀትና መዋቅር መፍጠር የሪፎርሙ ትግበራዎች ዋነኛ ማጠንጠኛዎች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
የለውጡ መንግስት ስኬቶች ከዘርፉ ባለፈ የሀገሪቱን የወል ትርክት በመቅረጽ ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቢኒያም ኤሮ በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግሥት በዘርፉ ያደረገው ሪፎርም ኮርፖሬሽኑ የነበሩበትን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መፍታት ማስቻሉን ገልጸዋል።
እንዲሁም ተቋሙ ዓበይት የለውጥ እመርታዎችን እንዲያሳይ በር ከፋች እንደነበር ተናግረዋል።
መዋቅራዊ ክፍተቶች፣ ግልጽ ያልሆነ ኤዲቶርያል ፖሊሲ፣ የብዝሃነትና ተደራሽነት ፈተና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ኋላ ቀርነት ተቋሙን የፈተኑት ማነቆዎች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ለውጡ እነዚህን ተግዳሮቶች ደረጃ በደረጃ ለይቶ በማረም ስኬቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል ብለዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል በርከት ያሉ ስቱዲዮዎችን በክልል ከተሞች ማስፋፋት፣ የዲጂታል ሚዲያ ተፎካካሪነትንና ዓለምአቀፍ የሚዲያ አጋርነትን ማጠናከር፣ የሀገርኛ ቋንቋዎች ይዘት ስርጭትን በመጨመር ተደራሽነትን ማስፋት ከብዙ ጥቂቶቹና ዋነኞቹ ስኬቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የለውጡ መንግስት ያስመዘገባቸው ስኬቶችን ለተቋሙ ጥልቅ አበርክቶ አድርጓል ያሉት ደግሞ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው ናቸው።
ተቋሙ ሰፊውን ሪፎርም በመቀላቀል ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሙያዊ ነጻነቱ የተከበረ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በይዘት፣ በተለወጠ አደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ አማራጮች ተደራሽ በመሆን ተወዳዳሪነቱን ማስፋቱን ገልጸው፤ ተቋሙ ከሪፎርሙ በመቋደሱ ከራሱ አልፎ ሰፊ የብሮድካስት ልምዱን በማካፈል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።