ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የጋራ ማንነትን የሚገነቡና ለሀገራዊ  ግቦች በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው  - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)


አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የጋራ ማንነትን የሚገነቡና ለሀገራዊ ግቦች በቁርጠኝነት  የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት "የሚዲያ  እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በለውጡ ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በተደረገው ሪፎርም የሚታይ ለውጥ ተመዝግቧል። 


የለውጡ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና ነፃና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ለመፍጠር በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን መፍታት የመጀመሪያው እርምጃ እንደነበር አስታውሰዋል።


በሙያቸው ምክንያት ተዘግተው የቆዩና ወደ ሀገር ቤት ገብተው እንዳይሠሩ የተከለከሉ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ወደ ሀገራቸው መጥተው እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸዋል ብለዋል። 


ከዚህም ባለፈ በመገናኛ ብዙሃን ሪፎርሙ ከውጭ ሆነው የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን ይጠለፉ (ጃም ይደረጉ) የነበረበትን አሠራር ማስቀረት እንደተቻለ ጠቁመው፤ በለውጡ መንግሥት የፀረ-ሽብር አዋጁን ጨምሮ ሌሎች አሳሪ ሕጎች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል ብለዋል።


ይሁን እንጂ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ሲከፈት ወደ ሙያው ለመግባት የተቸገሩና ነፃነታቸውን ማስተዳደር ያልቻሉ ባለሙያዎች በመፈጠራቸው ለዘርፉ ፈተና እንደሆኑ ገልጸዋል። 


በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ባይፈቱም መልካም ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ያዩትንና የሰሙትን እውነት የሚዘግቡ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃን የጋራ ማንነትን የሚገነቡ መሆን አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለዚህም ቅንጅትና ትብብርን በማጠናከር ለውይይትና ንግግር አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የሌሎችም ዘርፎች ዋልታ ረገጥነት ቀርቶ ሚዛናዊነት መንገስ እንዳለበትም አሳስበዋል።


ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በቂ ጥላቻ፣ መናናቅና መከፋፈል ተዘርቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አሁን መገናኛ ብዙሃን  በአንድነትና የተሳሳቱ ትርክቶችን ማቅናት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ገልጸዋል። 


መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ዓላማን፣ አተያይን፣ ሙያዊ ብቃትን እንዲሁም ቅርበትን መሠረት አድርገው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም