ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን የሪፎርም ስራዎች የግሉ ሚዲያ ሀገርን በመገንባት ሂደት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙሃን የሪፎርም ስራዎች የግሉ ሚዲያ ሀገርን በመገንባት ሂደት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻሉን የግል ሚዲያ ተቋማት አመራሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡


 

የናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (NBC) ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያ የግል የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሀገር ብሄራዊ ጥቅም በጠበቀ መልኩ ከመስራት አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው አውስተዋል።

በለውጡ መንግሥት የትኛውንም የአስተሳሰብ ልዩነት በኢትዮጵያ ጥላ ስራ ማራመድ ይቻላል የሚል እሳቤ እንዲገነባ የተደረገበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

በዚህም በመገናኛ ብዙሃን ላይ የህግ እና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጉን በመጠቆም ይህም በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወደ ሀገሪቱ ገብተው በመስኩ መሰማራት የሚችሉበትን ምቹ መደላድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

በተለይም በዘርፉ ላይ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ለስራቸው ከውጭ የሚያስገቧቸው የሥራ መሳሪያዎች ላይ ሲጣል የነበረው ከፍተኛ የሆነ ታክስ እንዲቀንስ መደረጉ በመስኩ ላይ መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል።

በሀገሪቱ የመረጃ ነጻነት ህግ ቢኖርም መረጃ ሰጪዎች ይህን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች እንዳሉባቸው በመግለጽ ይህ ሊቀረፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

የአዋሽ ኤፍ ኤም ዋና ስራ አስኪያጅ አብዱ መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች አሁን ካለው ማህበራዊ ሚዲያ ጋር አብሮ መራመድ የሚያስችላቸውን አቅም ለመፍጠር ተቋማዊ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም ገቢን ለማግኘት የሚሄዱበት መንገድ ከስነ-ምግባር እና ከሀገራዊ ጥቅምን ከመጠበቅ አንጻር ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

የግል የንግድ የሬዲዮ ጣቢያዎች በሚዲያው ዘርፍ ጠንካራ ሆነው እንዲዘልቁ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊው እገዛን ይሻሉ ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባቸው በመጠቆም ይህ ሲሆን ዘመኑን የሚመጥን የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ እውን ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም