ቀጥታ፡

ከለውጡ ወዲህ በሕዝብና በግል መገናኛ ብዙኃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር የመስራት ባህል እየዳበረ መጥቷል

‎አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በሕዝብና በግል መገናኛ ብዙኃን መካከል በሀገር ሰላም፣ ልማት፣ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ በትብብር የመስራት ባህል እየዳበረ መምጣቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) በተገኙበት “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ መድረክ ተካሂዷል፡፡ 

ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ሪፎርም ካደረገባቸው አንኳር ጉዳዮች አንዱ የሚዲያ ዘርፉ ሲሆን፥ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የሚዲያ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ነበሩባቸው። 

በሚዲያ ሪፎርሙ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍን ጨምሮ የሚዲያ ምህዳር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት  የሚዲያ ምህዳሩን ለማስፋት በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱንም ተናግረዋል።

የሚዲያ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን የሚዲያ ምህዳር በሙያዊ ሥነ-ምግባር እና በዲሞክራሲያዊ አደረጃጀት ለመቅረጽ ትልቅ መሰረት መጣሉም አመላክተዋል።

ሪፎርሙን ተከትሎም ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን በማንሳት፥ የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓት መፍጠር፣ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ማቋቋም እንዲሁም የሙያ ማህበራት ማበራከትን በአብነት ጠቅሰዋል።

በዚህም ‎የውጭ ሚዲያዎችና የማህበረሰብ ሚዲያዎች ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ የሬዲዮና የቴሊቪዥን ጣቢያዎች በብዛትና ተደራሽነት ላይ ዕድገት ማሳየታቸውን  የመገናኛ ብዙኃን  ቁጥር ወደ 310 ማደጉን አስረድተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት  የቋንቋ ተደራሽነት መስፋፋት መቻሉን ገልጸው፤  አሁን ላይ በ60 ቋንቋዎች መረጃን ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የሚዲያ ምህዳር አካታችነትን በመፍጠር ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ለውጡ በሚዲያ ዘርፍ በርካታ ትሩፋቶችን ማምጣቱን ገልጸው፥ መንግሥት  በሰጠው ትኩረትና ባደረገው ድጋፍ የሚዲያ ተቋማቱ አቅም መጎልበቱን ተናግረዋል።

በዚህም መገናኛ ብዙኃኑ በሀገር ሰላም፣ ልማት አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው በትብብር የመስራት ባህላቸው እየዳበረ መምጣቱን ነው ያነሱት።

ይሁን እንጂ አሁንም የዲጂታል ሚዲያ አሉታዊ ተፅዕኖ፣ የጋዜጠኝነትና አክቲቪስትነት መደበላለቅና ከብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ የመቆም ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የሚዲያ ሪፎርሙን በማስፋት በተለይ በዲጂታል ሚዲያው የሚስተዋሉ ነጻነትን ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር በተናበበ መልኩ ያለመጠቀም ችግሮችን ለማረቅ እንደሚሠራ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የፖሊሲ ትግበራን ማስፋትና ሙያዊ አቅምን ማሳደግም የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም