በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
ሰቆጣ፤ ሚያዚያ 29/2018 (ኢዜአ)፡-በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ የታቀዱ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በመፈፀም አበረታች ውጤት መመዝገቡን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት አፈጻጸምን የሚገመግም መድረክ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን እንዳሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰላም በማስፈን ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ሥራዎች የተመቸ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል።
በዚህም በተቀናጀ አግባብ በተከናወኑ ሥራዎች የአካባቢውን ልማት ማፋጠን እንደተቻለ ጠቅሰው፣ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁትን 77 የትምህርትና የጤና ተቋማት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በህብረተሰቡ ተሳትፎ በቅንጅት መስራት በመቻሉ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሁሉም ዘርፍ አበረታች ውጤት መመዝገቡንም አቶ ሹመት ገልፀዋል።
በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም በማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋትና ወረርሽኝን ለመከላከል የተሰሩት ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰቡ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ ናቸው።
በህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ የቆየው የአስ ከተማ ሆስፒታል ግንባታ ከነበሩበት ውስብስብ ችግሮች በማውጣት ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የህብረተሰቡን የጤና መድህን ተጠቃሚነት በማሳደግ በአራት ወረዳዎች ላይ የማህበረሰብ አቀፍ መድሀኒት ቤቶች መቋቋማቸውን ተናግረዋል።
የሰቆጣ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በከተማው ሰላምን በመጠበቅ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ በ129 ሚሊዮን ብር በጀት 17 ፕሮጀክቶች በከተማው እየተገነቡ መሆኑን ገልፀው፤ በራስ አቅም የኮሪደር ልማት ሥራም ተጀምሯል ብለዋል።
በሰቆጣ ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው በዚህ መድረክ የአስተዳደሩን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈ ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ተመላክቷል።