የፖሊሲ ማሻሻያው የሬዲዮ ጣቢያዎች ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊሲ ማሻሻያው የሬዲዮ ጣቢያዎች ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት ሪፎርም የሬዲዮ ጣቢያዎች የጋራ እሴቶችን በማጠናከር፣ ማህበረሰብን በማስተሳሰር እና ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ማስቻሉን የአዋሽ ኤፍ ኤም ዋና ስራ አስኪያጅ አብዱ መሀመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
የአዋሽ ኤፍ ኤም ዋና ስራ አስኪያጅ አብዱ መሀመድ(ዶ/ር) ''የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ'' በተሰኘው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ ያበረከታቸውን ትሩፋቶች አብራርተዋል።
የቁጥጥር እና የፖለቲካ ገደቦች፣ የአቅምና የሙያ ክፍተቶች፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ገደቦች ዘርፉንና ተቋሙን ሲፈትኑ የከረሙ ስር የሰደዱ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።
እነዚህ ችግሮች የፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ትኩረት በመስጠት መፈታታቸውን ገልጸዋል።
ይህም የሬዲዮ ጣቢያዎች ከመበራከታቸው ባለፈ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር፣ ማህበረሰብን በማስተሳሰር እና ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ማስቻሉን ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።