ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ በንፅህና አጠባበቅ እና በኢነርጂ ዘርፎች ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ በንፅህና አጠባበቅ እና በኢነርጂ ዘርፎች ያስመዘገባቸውን ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት ሪፖርት፤ በገጠርና ከተማ በተገነቡ 3 ሺህ 278 የመጠጥ ውሃ ተቋማት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ79 ሚሊየን 593 ሺህ ወደ 82 ሚሊየን በላይ ማድረስ ተችሏል።

የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ከ1 ነጥብ 600 ሺህ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገትና የዜጎችን ፍላጎት ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

በዘጠኝ ወራቱ በውሃ ሽፋን፣ በሳኒቴሽንና በኢነርጂ ዘርፎች ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማና አበረታች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በንፁህ መጠጥ ውሃ እና ኢነርጂ ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት አልፎ አልፎ እንቅፋት የሆኑትን የጥናትና የዲዛይን ሥራዎች ጥራት መጓደል በዘላቂነት ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዲብራሩ ጠይቀዋል፡፡

በስምጥ ሸለቆ የሚስተዋለውን የፍሎራይድ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚታየውን የአይረን ይዘት ከፍተኛ መሆን በዘላቂነት ለመፍታት የታቀዱ ቀጣይ ዕቅዶች እንዲብራሩም ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ የሚስተዋለውን የፍሎራይድ እና የአይረን ችግሮች የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘዴዎችን በመጠቀም ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የውሃ ፕሮጀክቶች መዘግየት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ከከተሞች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ አህመድ፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በሳኒቴሽንና በኢነርጂ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡

በገጠርና በከተማ የውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ከዕቅድ በላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይህ ስኬት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ስራው የዜጎችን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም