በክልሉ ሙስናን የመከላከል ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሙስናን የመከላከል ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል
ቦንጋ፤ ሚያዚያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሙስና መከላከል ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የ2018 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማና የቀጣይ ሶስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል ።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
ሙስናን በመከላከሉ ረገድ መልካም ተግባራትን እየፈፀመ መሆኑን ያነሱት አፈ ጉባኤው፣ መፈፀም ሲገባቸው ያልተፈፀሙ ጉዳዮችን በዝርዝር ለይቶ በትኩረት ወደ ተግባር መግባት ይገባዋል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ሙስናን የመከላከል ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ከፖሊስ፣ ፍትሕና ሌሎች አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።
የቀረቡ ጥቆማዎችን መከታተልና የህግ ተጠያቂነትን የማስፈን ተግባሩን ሊያጠናክር እንደሚገባም አመልክተዋል ።
የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍትሕና ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት በሀብት ጥበቃ፣ በስነ-ምግባር ግንባታና በሙስና መከላከል ረገድ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በዚህም በየጊዜው ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ጥቆማዎች ቁጥር እንዲጨምርና የተቋሙ ውጤታማነትም እንዲያድግ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 729 የሙስና ጥቆማዎች በየደረጃው ወደ ኮሚሽኑ መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም በአስቸኳይ ሙስና መከላከልና በኦዲት ግኝት 140 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የመንግስት ሀብትና ንብረት ማዳንና ማስመለስ መቻሉን አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የከተማና የገጠር መሬትን ጨምሮ ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከምዝበራ ማዳን መቻሉንም ዋና ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ የሀብት ምዝገባ ስራ ውጤታማነትና በዲጅታል ስርዓት ትግበራ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ጨምሮ አስር ዋና ዋና ግቦችን የያዘውን የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የሙስና መከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ የአመራሩ ቁርጠኝነት ሊጠናከር ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ሰብስቤ ሻዎኖ ናቸው።
ኮሚሽኑ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራውን አጠናክሮ ሊስቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።