ቀጥታ፡

የሪፎርም ስራው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሙያዊ ነጻነቱ የተከበረ እንዲሆን አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት ሪፎርም ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሙያዊ ነጻነቱ የተከበረ ማድረግ ማስቻሉን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው ''የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ'' በተሰኘው የዘርፉ የምክክር መድረክ ላይ በሚዲያው ዘርፍ የለውጡ መንግስት ያስመዘገባቸው ስኬቶችን ለተቋሙ ያለውን አበርክቶ በጥልቀት አቅርበዋል።

ተቋሙ ሰፊውን ሪፎርም በመቀላቀል ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሙያዊ ነጻነቱ የተከበረ ማድረግ መቻሉን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በይዘት፣ በተለወጠ አደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ አማራጮች ተደራሽ በመሆን ተወዳዳሪነቱን ማስፋቱን የጠቀሱት አቶ አድማሱ፤ ተቋሙ ከሪፎርሙ በመቋደሱ ከራሱ አልፎ ሰፊ የብሮድካስት ልምዱን በማካፈል ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በመጨረሻም ፈጠራን፣ የሀሳብ ብዝሀነትና አለም አቀፋዊነትን በማስፋት ተመራጭና ወቅታዊ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም