ቀጥታ፡

የለውጡ መንግስት ሪፎርም ኢዜአን ዳግም እንዲወለድ አድርጎታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት ሪፎርም ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዳግም እንዲወለድ አድርጓል ሲሉ የተቋሙ ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ''የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ'' በተሰኘው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከምስረታው ባልተናነሰ የለውጡ መንግሥት በዘርፉና በተቋሙ ባደረገው ሪፎርም ምክንያት ዳግም ተወልዷል ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል።

በተቋሙ የተከናወነው የእሳቤ፣ የህግና አደረጃጀት እንዲሁም የአሰራር ሪፎርም፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በአፍሪካ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ በመሆን ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅና ብሄራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል አቅም እንዲላበስ አስችሎታል ብለዋል።

በተጨማሪም ተቋሙ ተደራሽነቱን በማስፋትና በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ፣ ከኢትዮጵያ ተሻግሮ የአፍሪካ ድምጽ በመሆን የወል ትርክትን እየገነባ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም