የድሬዳዋ ወጣቶች ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ የከተማዋን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል አስተዋፅኦ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ወጣቶች ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ የከተማዋን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል አስተዋፅኦ እያደረገ ነው
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ወጣቶች ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ የከተማዋን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር አባላት በልማትና በፀጥታ ማስከበር እያከናወኑት ላለው አርያነት ያለው ተግባር እውቅና ተሰጥቷል።
የአስተዳደሩ ከንቲባና የፀጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢ ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወጣቶች በልማትና በሰላም ማስፈን ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ ነው።
የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር ወጣት አባላትም ከፍትህና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የከተማና የአካባቢው ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ እንዲሁም የማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የማህበሩ አባላት ደም በመለገስ፣ ማዕድ በማጋራት፣ በታክሲ ወስጥ የጠፉ ንብረቶችን በታማኝነት በመመለስ በኩል በአርአያነት የሚጠቀሱ ሥራዎችን እንዳከናወኑም አመልክቷል።
እነዚህ የወጣቶቹ መልካም ሥራዎች እንዲጠናከሩ አስተዳደሩ እውቅናና ሽልማት ማበርከቱንም ከንቲባ ከድር አንስተዋል።
የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ኢብራሒም ዩሱፍ በበኩላቸው ወጣቶቹ "ለሊቱ የኛ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በመመራት ለድሬዳዋ ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ አጋዥ ሆነዋል።
ወጣቶቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡና የድሬዳዋን ገፅታ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ገንዘብ፣ እውቀት፣ ሙያና ጊዜያቸውን በመለገስ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወጣቶቹ የሕጻናትና የእናቶችን ሕይወት ለመታደግ ለ17ኛ ጊዜ ደም እንደለገሱና በየዓመቱም አቅም ለሌላቸው 500 ተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ቁሶች እየደገፉ መሆኑን አስታውሰዋል።
ወጣቶቹ hገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለድሬዳዋና አካባቢው ሰላምና ልማት ተጠቃሽ ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ናቸው።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው የታክሲ አሽከርካሪዎቹ የህብረተሰቡን ባህል፣ ወግና ኃይማኖታዊ ስርአት ባከበረ መንገድ ህዝብን እያገለገሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ወጣቶቹ ለአቅመ ደካሞች ነፃ አገልግሎት በመስጠትና አረጋውያንን በመደገፍ እያደረጉት ያለው በጎ ሥራ በአርአያነት እንደሚጠቀስም ተናግረዋል።
የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ቃልኪዳን ፀሐይ እና ባልደረቦቹ የተሰጣቸው እውቅናና ሽልማት የበለጠ ተግተው እንዲሰሩ ብርታት እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።