የመንግስት የሪፎርም ስራ ለኢቢሲ የለውጥ እመርታዎች በር ከፋች ሆኗል - የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቢኒያም ኤሮ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የሪፎርም ስራ ለኢቢሲ የለውጥ እመርታዎች በር ከፋች ሆኗል - የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቢኒያም ኤሮ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የመንግስት የሪፎርም ስራ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የለውጥ እመርታዎች በር ከፋች መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቢኒያም ኤሮ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቢኒያም ኤሮ፤ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሚዲያ ታሪክ ፈር ቀዳጁና የጥንቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የነበሩበትን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ለመፍታት የለውጡ መንግሥት በዘርፉ ያደረገው ሪፎርም ተቋሙ ዓበይት የለውጥ እመርታዎችን እንዲያሳይ በር ከፋች ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
መዋቅራዊ ክፍተቶች፣ ግልጽ ያልሆነ ኤዲቶርያል ፖሊሲ፣ የብዝሃነትና ተደራሽነት ፈተና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ኋላ ቀርነት ተቋሙን ሲፈትኑት የነበሩ ማነቆዎች እንደነበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።
ለውጡ እነዚህን ተግዳሮቶች ደረጃ በደረጃ ለይቶ በማረም ስኬቶችን ማስመዝገቡን የጠቀሱት አቶ ቢኒያም፤ ከእነዚህም መካከል በርከት ያሉ ስቱዲዮዎችን በክልል ከተሞች ማስፋፋት እንዲሁም የዲጂታል ሚዲያ ተፎካካሪነትንና ዓለም አቀፍ የሚዲያ አጋርነትን ማጠናከር ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም የሀገርኛ ቋንቋዎችን በመጨመር ተደራሽነትን ማስፋት የተቻለ ሲሆን፤ እነዚህም ከተመዘገቡት በርካታ ስኬቶች መካከል ጥቂቶቹና ዋነኞቹ መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።