በአማራ ክልል የፍትህ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ለሰው ኃይል አቅም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፍትህ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ለሰው ኃይል አቅም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል
ባህርዳር፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት የመስጠት ስራውን ለማጠናከር ለሰው ሀይል አቅም ግንባታ ስራ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው አስታወቁ።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር የዳኞችን አቅም ለመገንባትና በጋራ ለመስራት ያለመ የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ ተፈራርመዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዓለምአንተ አግደው በወቅቱ እንደገለፁት፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰው ኃይሉን አቅም፣ ዕውቀትና ክህሎት ማሳደግ የሚያስችለውን የሪፎርም ስራ ተግባራዊ አድርጓል።
የስምምነቱ ዋና አላማም ዳኞችና የፍትህ ባለሙያዎች የወጡ የካፒታል ገበያ ህጎችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን ተገንዝበው የተቀላጠፈና ወጥነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ስምነቱ ከአክሲዮን ገበያ ጋር በተያያዘ ግልፅነት ያለው አሰራር እንዲዳብር፣ የዜጎች ንብረት እንዲከበርና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል።
ይህም የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞችን ከዳኝነትና የፍትህ ዘርፉ የትራንስፎርሜሽን ጋር በማጣጣም መስራት እንደሚያስችል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ የካፒታል ገበያ ስርዓትን በህግ ዕውቀት ተደግፎ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ህግና ዓለምአቀፍ የህግ ማዕቀፎችን መሰረት በማድረግ የህግ ትርጓሜ መስጠት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
ከጋራ የመግባቢያ ሰነዱ ፊርማ በኋላም ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍትህ ቢሮ፣ ከፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት የተውጣጡ ባለሙያዎች በካፒታል ገበያ የህግ ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ታውቋል።