ማህበሩ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚናውን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚናውን እየተወጣ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማህበሩ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ማህበር ገለፀ።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወጣት ሰላማዊት ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለፀችው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶችን የላቀ ሚና ለማሳደግ አየተሰራ ነው።
ለዚህም ማህበሩ "የወጣቶች ተሳትፎ ለሰላማዊ ምርጫ" በሚል መሪ ሃሳብ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማካሄዱን ተናግራለች።
ወጣቱ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ከማድረግ አንፃር ግንዛቤ በመፍጠር ውጤታማ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ምርጫውን የሚታዘቡ ከ600 በላይ ወጣቶች መዘጋጀታቸውን ገልጻለች።
የወላይታ ዞን ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ምህረቱ ዳና በበኩሉ እንደገለጸው፤ በዞኑ የወጣቱን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ወጣት እንሹ ባፋ በበኩሏ፤ እንደ ወጣት በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ሀገርን የማጽናት ኃላፊነቷን ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልጻለች።