የለውጡ መንግስት የሚዲያ ተቋማት የነበሩባቸውን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ለማከም ጥልቅ የሆነ የሚዲያ ሪፎርሞችን አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግስት የሚዲያ ተቋማት የነበሩባቸውን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ለማከም ጥልቅ የሆነ የሚዲያ ሪፎርሞችን አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት የሚዲያ ተቋማት የነበሩባቸውን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ለማከም ጥልቅ የሆነ የሚዲያ ሪፎርሞችን ማድረጉን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ከለውጡ በፊት የሚዲያ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ነበሩባቸው።
ከነዚህም ጥቂቶቹ የፖሊሲ እና የማዕቀፍ ፣ የመዋቅር አደረጃጀት፣ ተቋማዊና የትክክለኛ ሙያዊ ስነ-ምግባር ስብራቶች እንደሚገኙበት ነው የገለጹት።
የለውጡ መንግስት እንዚህን ስብራቶች ለማከም ጥልቅ የሆነ የሚዲያ ሪፎርሞችን ማድረጉንም አብራርተዋል።
ሪፎርሙ ካሳካቸው ለውጦች መካከልም ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ የመገናኛ ብዙሃን ባልስልጣን ማቋቋም፣ የመገናኛ ብዙሃን የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓት መፍጠር፣ እንዲሁም ዘርፉ እራሱን በራሱ እንዲቆጣጠር የሚያስችሉ የሙያ ማህበራትን ማበራከት ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።
ሪፎርሞች ትክክለኛ ውሳኔዎች ስለመሆናቸው በተመለከተም የመገናኛ ብዙሃን አሃዛዊ ስኬቶች ከለውጡ በፊት ከነበሩበት 122 ወደ 310 ከፍ ብሏል፣ የሬድዮ ጣቢያዎች ከለውጡ በፊት ከነበሩበት 52 ወደ 126፣ የቴለቪዥን ጣቢያዎች ከለውጡ በፊት ከነበሩበት 25 ወደ 128፣ የመገናኛ ብዙሀን የቋንቋ ተደራሽነት ከለውጡ በፊት ከነበሩበት 39 ወደ 60 ማደጉን አብራርተዋል።
እንዲሁም 35 የውጭ ሚዲያዎችና 50 የማህበረሰብ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ የሚዲያ ምህዳር አካታችነትን በመፍጠር ላስመዘገበው ስኬት አይነተኛ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።