የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የሀገሪቱን መጻዒ እድል ብሩህ የሚያደርጉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የታዩበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የሀገሪቱን መጻዒ እድል ብሩህ የሚያደርጉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የታዩበት ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የሀገሪቱን መጻዒ እድል ብሩህ የሚያደርጉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የታዩበት መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አራተኛውን የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ ጎብኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በኤክስፖው የሀገሪቱን መጻዒ እድል ብሩህ የሚያደርጉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማጠናከር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ በኩል ተጨባጭ ውጤቶች የታዩበት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት እያመረተች መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቆንፅላዎችና የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች የሀገር ውስጥ ምርቶችን በአምባሳደርነት የማስተዋወቅና ሰፊ የገበያ እድሎችን የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ኤክስፖው የሀገር በቀል ምርቶችን አቅም ለዓለም ከማሳየት ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚያዝያ 25 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን አራተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል።