ቀጥታ፡

የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ኬላ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ርዕሰ መስተዳድሩ በሚወዳደሩበት ምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳና እጩ የማስተዋወቅ መርሐ ግብር ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችንን ሲያከናውን ቆይቷል።

በባለፉት የለውጥ ዓመታት የሀገርን እድገትና የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለይ በከተማና በገጠር ዘመናዊ አሰራርን ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ ፓርቲው ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ ኢትዮጵያን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ህዝቡ ከፓርቲው ጎን ሊቆም እንደሚገባም እንዳሻው (ዶ/ር) አመልክተዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው እንዳሉት፤ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን አስመዘግቧል።


 

በተለይም  የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆኑት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራ ዞኑ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ እንዲጠቀም አስችሎታል ብለዋል።

ኢኒሼቲቮቹ የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው፣ በዞኑ እየታየ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ህብረተሰቡ ከፓርቲው ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በቅስቀሳ መርሃ ግብሩ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም