ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶችን ከሳይንሳዊ ምርምር ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶችን ከሳይንሳዊ ምርምር ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቷል
ሮቤ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከሳይንሳዊ ምርምር ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መስጠቱን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ሀገር በቀል እውቀቶች ከሳይንሳዊ ምርምር ጋር ለማገናኘት ዓላማ ያደረገና በአይነቱ ልዩ የሆነ የአርሶ አደሮች የምርምር ኮንፈረንስ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ተግባሩ በተጓዳኝ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል የሚያግዙ የግብርና ግብዓቶችንና የተሻሻሉ አሰራሮች በማቅረብ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኮንፈረንሱ በተለይ በዋናነት አርሶ አደሮች ያላቸውን ተፈጥሯዊና በልምድ የተገኙ እውቀቶችን ወደ መድረክ በማውጣት እውቅና ለመስጠትና ለቀጣይ የምርምር ሥራዎች ግብዓት እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም መድረኩ በአርሶ አደሩ፣ በተመራማሪዎች እና በዘርፉ ባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ የግንኙነት ድልድይ በመፍጠር ልምድ ለመለዋወጥ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
ሀገር በቀል ጥበቦችን ከዘመናዊ የግብርና ሳይንስ ጋር በማቀናጀት የምርት ጥራትንና ብዛትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር በላይ ስመአኒ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተግባር በተጓዳኝ በተለይ አርሶ አደሩን ከዘመናዊ የግብርና አሰራር ጋር ይበልጥ ለማላመድ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።
በተለይ አርሶ አደሮች ያላቸውን ሀገር በቀል እውቀት ወደ መድረክ በማምጣት ልምድ እንዲለዋወጡ የተዘጋጀው የምርምር ኮንፈረንስ ልዩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
መድረኩ በተለይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘው ሀገራዊ ግብ እንዲሰምር ሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ምርምር ጋር ለማገናኘት የተጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል።
መድረኩ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በግብርና፣ በእንስሳት እርባታና በሌሎች መስኮች ልምዳቸውን በማቅረብ ለሌሎች አርሶ አደሮች ልምድ የሚያካፍሉበት ዕድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ተመራማሪዎች በአርሶአደሩ ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ምርምር የሚያደርጉበትን ግብአት ለማግኘት ያስችላቸዋል ሲሉ ነው የገለጹት።
በኮንፈረንሱ ላይ አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የአርሶ አደሮች ምርት አውደ ርዕይ እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል።