ቀጥታ፡

በዞኑ በመጪው ክረምት የሚተከሉ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል

ጋምቤላ ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በማጃንግ ዞን በዘንድሮው ክረምት የሚተከሉ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ግብይት ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በዘንድሮው ክረምት ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ከ4 ሚሊዮን 260 ሺህ የሚበልጡ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የቡና ችግኞቹ በፕሮጀክቶች፣ በባለሃብቶችና በአርሶ አደሮች የተዘጋጁ ሲሆን ከአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ጋር በማስተሳሰር የሚተከሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በክረምቱ ወቅት ሀገር በቀል የጥላ ዛፎች በጥምርና በተጎዱ አካባቢዎች የሚተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ለተከላ የተዘጋጁት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምርና እውቅና ከተሰጣቸው ዘር አዘጋጅ ማህበራት የተገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሄክታር ከ10 ኩንታል በላይ የሚሰጡት እነዚሁ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ቀደም ሲል ከነበሩት ጋር ሲነፃፀር በሁለት ኩንታል ብልጫ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

በዞኑ ያረጁና ምርታማ ያልሆኑ የቡና ዝርያዎችን በተሻሻሉት የቡና ዝርያዎች በመተካት ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱንም ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅትም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ነው ቡድን መሪው ያመለከቱት።

በዞኑ የጎደሬና የመንጌሽ ወረዳዎች በአርሶ አደሮችና በባለሃብቶች ከ71 ሺህ 160 ሄክታር በላይ መሬት በቡና መልማቱንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም