ጉባኤው የአህጉሪቱን እውነተኛ ገጽታ ለማስተዋወቅ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው የአህጉሪቱን እውነተኛ ገጽታ ለማስተዋወቅ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ የአህጉሪቱን እውነተኛ ገጽታ ለማስተዋወቅና የለውጥ ትርክትን ለመገንባት ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን በባለቤትነት ለመምራት ያለመው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል።
በጉባኤው ለመታደም ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 321 ሚሊዮን በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ያሏቸው 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በአዲስ አበባ ከትመዋል።
በተጨማሪም 150 ሚሊዮን ተከታዮች ያላቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች በጋራ በመሰባሰብ፣ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ ተዘጋጅተዋል፡፡
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ /pulse of Africa/ ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ጉባዔ "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" የሚል መሪ ሀሳብ ይዟል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ከአራቱም የአህጉሪቷ ማዕዘናት በመምጣት በውቧ አዲስ አበባ ከትመው የተለየዩ ሥራዎችን መጎብኘት ጀምረዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ከኬንያ የመጣው ወጣቱ ሳሙኤል ማቦቴ፣ አዲስ አበባን "ውብና በእርግጥም የአፍሪካ ዋና ከተማ" በማለት ገልጾ፣ በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ በመሳተፉ የተሰማውን ኩራት ገልጿል።
በመላው አፍሪካ የሚገኙ የይዘት ፈጣሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን ይህን መድረክ ላዘጋጁት አካላት ምስጋናውን ያቀረበው ሳሙኤል፤ ማህበራዊ ሚዲያ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን በመሆኑ፣ ወደዚህ ዘመናዊ ምዕራፍ መሸጋገር አለብን ብሏል፡፡
አፍሪካን ለመገንባትና ለመለወጥ ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከመላው ዓለም ከመጡ የይዘት ፈጣሪዎች ጋር ለመገናኘትና ልምድ ለመለዋወጥ መዘጋጀቱን ጠቅሷል፡፡
አፍሪካን በአዲስ ተስፋ ለመገንባትና ለመለወጥ መሰል መድረኮች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሷል፡፡
ከካሜሩን የተገኘው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ሞስቲክ ካሪስማቲክ በበኩሉ፤ ጉባኤው ድንቅ ሀሳብን የያዘ መሆኑን ገልጿል።
እንዲሁም ከአፍሪካውያን ወንድም እና እህቶች ጋር ለመተዋወቅ ትልቅ እድልን የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል።
ጉባኤው ሀሳቦችን በማጣራት ጠንካራ አፍሪካን ለመገንባትና ጠንካራ የወጣቶች ተፅዕኖ ለመፍጠር ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን አንስቷል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ብራድሊ ማሮንጎ በአዲስ አበባ መገኘቱ በጣም እንዳስደሰተው ጠቅሷል፡፡
አዲስ አበባን በጣም ምርጥ ከተማ በማለት ያሞካሸው ወጣቱ የይዘት ፈጣሪው፣ አብሮ ለመስራትና ልምድ ለመለዋወጥ በሙሉ ፈቃደኝነት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።